የዜጎችና የሃይማኖት ነፃነት ያለምንም ጣልቃ-ገብነት ይከበር!!

የዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) የአቋም መግለጫ።

የዜጎችና የሃይማኖት ነፃነት ያለምንም ጣልቃ-ገብነት ይከበር!!

ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) ለረዥም ጊዜያት የኢትዮጵያውያን መብት ሳይሽራረፍ እንዲከበር ብዙ አስተዎፅዖ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። በተለይ ለውጥ መጥቷል በተባለበት ጊዜ ሳይቀር አለበቂ ማስረጃ በየእስርቤቱ ተወርውረው፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡና ጥፍታቸው ሳይረጋገጥ በእስር ቤቶች ውስጥ እንግልት ለሚደርስባቸው ዜጎች በመቆም መንግስት ያለአግባብ ዜጎችን ማሰርና ማስቃየቱ አግባብ አለመሆኑን በማስጠንቀቅ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብና የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ብዙ ግፊት አድርጓል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በአገራችን በቤተ እምነቶች ላይ እየደረስ ያለው ቃጠሎና ውድመት ለረዥም ጊዜ ተከባብሮና ተፈቃቅሮ የኖረውን የክርስትናና የሙስሊም ሃይማኖት ተከታይ ወገኖቻችንን ባህሪ የማይገልፅ በመሆኑ እጅግ በጣም አሳዝኖናል። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተክርስቲያናትን ማቃጠል አገልጋዮቿንና ምዕመናኑን ህይወት በመቅጠፍ የስላማዊ ዜጎችን አንጡራ ንብረታቸውን ያወደሙት እኩያን በአስቸካይ ለህግ ቀርበው አፋጣኝ ምርመራ ተካሂዶ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ህዝባዊ ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ እስካሁን መንግስት የተቀላጠፈ እርምጃ ወስዶ ውጤቱን ለህዝብ ባለማስታወቁ፣-

  1. በተለያዩ አካባቢዎች በእምነታቸውና በማንነታቸው ላይ ባነጣጠረ መልኩ መስዋዕትነት ለከፈሉ በተለይ ደግሞ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ሃያ ሁለት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የእምነት ተቋማቸውን ከአፍራሽ ሃይሎች እየተከላከሉ በነበሩ ሶስት ወጣት ምዕመናን ላይ ከመንግስት ታጣቂዎች በተተኮስ ጥይት ለተገደሉ የተስማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን በዚህ ድርጊት ከፍተኛ ሃዘንና ብስጭት የደረስባቸው ምዕመናን ያቀረቡት የአስቸካይ ፍትህ ጥያቄ አሁንም በቸልታ የሚታለፍ ከሆነ የሚያስከትለው መዘዝ እጅግ የሚያሳስበን መሆኑን በአፅኖዖት እየገለጽን የሚመለከተው የመንግስት አካል ቅድሚያ ትኩረት እንዲስጠው እናሳስባለን።
  2. ዓለም በቅርስነት የመዘገባቸውን ጨምሮ ታላላቅ በአላትን በሰንደቅ አላማው አጅቦ ለዘመናት ሲደረግ እንደኖረው ማክበር ሲገባው በክልሉ ልዩ ሃይሎችና በዘር በተደራጁ ወጣቶች የተፈፀመው ጥቃትና ጣልቃ ገብነት የዜጎችን የእምነት ነፃነት በይፋ የሚጥስ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆምና ወደፊትም እንዳይደገም ጥብቅ መመሪያ እንዲስጥ እናሳስባለን።
  3. በቅርቡ በሞጣ የተቃጠሉት መስጊዶችና ንብረቶች መውደማቸው አግባብነት የሌለውና ለዘመናት ተዋደውና ተከባብረው በሚኖሩት የሁለቱ እምነት ተከታይ ሕዝቦች መሃል ሆነ ተብሎ መለያየት እንዲፈጠር የተቀነባበረ ሴራ መሆኑ እጅግ የወረደና እጅግ የሚያሳዝን በመሆኑ ጥፋቱን ያደረሱት ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች ጉዳዩ ተጣርቶ በአስቸካይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እያሳስብን የዜጎች በስላምና በፍቅር መኖር የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች ተፅዕኖ ሳይደረግባቸው በነፃነት ማምለክ መቻላቸው ለሰላም አንድነትና ብልፅግና ከፍተኛ አስተዋፅዖ ከማድረጉም በላይ ለምንመኘው እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ወሳኝ መሆኑ ታውቆ መንግስት ለዜጎች የአምልኮ ነፃነት መከበር ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግና ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንዲታቀብ እንጠይቃለን::

ለዜጎች ሁለንተናዊ መብት ዘብ መቆም የመንግስት ተቀዳሚ ተግባርና ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነፃነት ለዘላለም ትኑር!!