ግሎባል አሊያንስ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።

ግሎባል አሊያንስ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።
አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብቶች ወይም ግሎባል አሊያንስ ድጋፍ ያደረገው በዋግ ህምራ ዞን አበርገሌ ወረዳ ዙሪያ ለሚገኙ 1113 ድጋፍ ፈላጊዎች እንዲሁም ድጋፍ የተደረገላቸው ሰቆጣ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቅኔ ጉባኤ ቤት፣አበርገሌ ምሥራቀ ፀሐይ ቅ/ሚካኤል ቅኔ ጉባኤ ቤት እና ሰቆጣ ዙሪያ ላይ ሳይዳ ደብረ ገሊላ ቅ/ ማርያም አንድነት ገዳም የጉባኤ ተማሪዎች ነው። ይህንን ደጋፍ ያስተባበረው ደግሞ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በማህበራት ማደራጃ የማህበረ ቅዱሳን ነው።
ሲያትል ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በማህበሩ አማካኝነት የላከው 500,000 ብር ሲታከልበት የድጋፉን መጠን ወደ 1.5 ሚሊዮን ብር ከፍ ያደርገዋል። የድጋፉ መጠንም 202 ኩንታል የምግብ ግብዓቶች ድጋፍ ሲሆን ግሎባል አሊያንስ ድጋፉን ያደረገው በአሜሪካ ሜኔሶታ የሚገኘው የርእሰ አድባራት ፀርሃ አርያም ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ምእመናና አገልጋዮች ያበረከቱትን ስጦታ በማስተባባር ነው። የድጋፉም አይነት ለዕለት ደራሽ አስፈላጊ የሆኑ ምግቦችን ያካተተ ነው። በአበርገሌ ወረዳ እና ዙሪያው የሚገኙ አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ ድርቅ እየተጠቁ ሲሆን በተጨማሪም በሰላም እጦት ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ተፈናቃዮችንም ጭምር የያዘ እና ሰፊ ድጋፎችን የሚሻ ሲሆን ግሎባል አሊያንስ እና አጋሮቹ ላደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ነው ተብሏል።
በተለይም በዚህ ወቅት አርሶ አደሩ በከፍተኛ የድርቅ ችግሮች ውስጥ የሚገኝበት እና የሚፈለገውን ያህል ድጋፍ ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ ግሎባል አሊያንስ እና አጋሮቹ መድረስ መቻላቸው ከፍተኛ ምስጋና ያሰጠዋል ያሉት የአበርገሌ ወረዳ ምክትል አስተዳደር አቶ ክብሩ ይስፋ መለሰ ናቸው። የአርሶ አደሩ ተወካዮችም በተለይም አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አሊያንስ ከዚህ ቀደም መሰል ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው ተቋሙ ሁልጊዜም በችግራቸው ስለሚደርስ በምርቃት የታጀበ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በማህበራት ማደራጃ የማህበረ ቅዱሳን ማህበርን ወክለው አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ አግአዚ አብርሐ በበኩላቸው ግሎባል አሊያንስ እና ሌሎች አጋሮች በድርቅ ለተጎዱ እና ድጋፍ ለሚፈልጉ የቅኔ ጉባኤ ቤቶች መድረስ መቻላቸው ትልቅ ዋጋ ያለው እና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችም እንዳሉት አስታውሰው ለተቋሟቱ ምስጋና አድርሰዋል።
በኢትዮጵያ አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብቶች ተወካይ በፍቃዱ አባይ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት ግሎባል አሊያንስ በኢትዮጵያ በተከሰቱ የተለያዩ ችግሮች ሰበብ በመላው ኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነ አስታውሰዋል። ግሎባል አሊያንስ ከተለያዩ ተቋማት የሚያሰባስባቸውን ገንዘቦች በተገቢው መንገድብለታለመለት አላማ በማዋል ለወገን ችግሮች ደራሽ መሆኑን ማስመስክሩንና በዚህም መሰል ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል። በዚህም በአሜሪካ ሜኔሶታ የሚገኘው የርእሰ አድባራት ፀርሃ አርያም ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ምእመናና አገልጋዮች በግሎባል አሊያንስ አማካኝነት እንዲደርስ በማድረጋቸው ምስጋና ያቀረበ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተደረገው ድጋፍም የመጨረሻው ሳይሆን የሚቀጥል መሆኑን እንዲሁም እንደ ችግሮቹ ስፋት በሌሎች የሀገራችን ክፍሎችም ተደራሽ መሆኑን ይቀጥላል ብሏል።
ከአበርገሌ ወረዳ ባሻገርም ከላይ በዝርዝር ለተጠቀሱት የቅኔ ጉባኤ ቤቶችም ያደረሱ ሲሆን በዚህ ድጋፍም ጉባኤ ቤቶቹ ያጋጠማቸውን እጥረት በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት እና በተለይም በክረምት ምክንያት ሊዘጉ የተቃረቡ የጉባኤ ቤቶችን ከመዘጋት እንደታደጋቸውና ይህንን ድጋፍም በተጠናከረ መንገድ ላደረጉት ግሎባል አሊያንስ እና አጋሮቹ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ገ/ማርያም ሙልጌታ ከሰቆጣ ማዕከል ማህበረ ቅዱሳን ተጠሪ ናቸው።
በአበርገሌ ወረዳ ብቻ በድርቁና በጸጥታ ችግሮች ምክንያት ከ67000 በላይ ድጋፍ ፈላጊዎች አሉ። እነዚህ ወገኖችም አሁንም የሌሎችን ድጋፍ እየጠበቁ ይገኛሉ።