ግሎባል አሊያንስ ከ1ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰብአዊ ድጋፍ አደረገ።
በአርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው አለም አቀፍ ትብብር ለሰብአዊያን መብት (ግሎባል አልያንስ)ድጋፉን ያደረገው ኢትዮጵያ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዛይ ጎፋ ወረዳ ከንች ሻቻ ጎዘዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት ናዳ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 250 ኩንታል የበቆሎ ዱቄት ነው።
በስፍራው በመገኘት ሰብአዊ ድጋፉን ያስረከበው በኢትዮጵያ የግሎባል አሊያንስ ተወካይ አቶ በፍቃዱ አባይ ሲሆን ድጋፉን የተረከቡት ደግሞ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ናቸው።
ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመተውን ድጋፍ ከተረከቡ በኋላ አስተዳዳሪው ባስተላለፉት መልእክትም ግሎባል አሊያንስ ከዚህ ቀደመም በሀገራችን በሚከሰቱ የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በማድረግ ለኢትዮጵያውያን ያለውን ደራሽነት አስታውሰው በዞኑ የደረሰው የመሬት መንሸራተት የሰዎችን ህይወት መቅጠፉንና ንብረት መውደሙ ያስከትለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ አሁንም ለወገኖቹ ደራሽነቱን በማሳየቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቅረበዋል። ሀዘናችንን ሀዘናችሁ አድርጋችሁ፣ህመማችንን ታማችሁ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ድጋፍ ለማድረግ በመቻላችሁ ያለንን አክብሮት እንገልጣለን።የተጎጂዎች ቤተሰቦችም ከፍ ባለ ስሜት ያስታውሱታል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።
የግሎባል አሊያንስ የኢትዮጵያ ተወካይ በፍቃዱ አባይም ድጋፉን ካስረከቡ በኋላ በተፈጠረው ድንገተኛ አደጋ የተሰማችውን ሀዘን ገልጸው። እንደ ባህላችን ሀዘን ለመድረስ እና በሀዘን የተጎዱ ወገኖችን ለማጽናናት በማሰብ ግሎባል አሊያንስ የላከውን ድጋፍ ይዘው መምጣታቸውንና የድርጅቱ የቦርድ አመራሮችና አባላትም በተፈጠረው ድንገተኛ አደጋ ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማቸው ተናግረዋል። አደጋው በድንገት የተከሰተ እንደመሆኑ ለዚህ ተብሎ የተያዘ በጀት ባይኖርም ግሎባል አሊያንስ ከወገኖቻችን ሀዘንና ጉዳት ምንም የሚበልጥ ጉዳይ የለም በማለት ይህንን አስቸኳይ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
በአርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አሊያንስ በኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያ ውጪ ኢትዮጵያውያን በሚያጋጥሟቸው የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ፈጥኖ በመደረስ ወገኖችን በማጽናናትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ከወገኖቹ ጎን የሚቆም አለም አቀፍ ተቋም ነው።