ስደተኞችን ከመስጠም አድኖ ባለፈው ሳምንት የኢጣልያዋ ደሴት ላምፔዱዛ አቅራቢያ መልህቁን የጣለው «ኦፕን አርምስ» የተባለው የስፓኝ የእርዳታ ድርጅት መርከብ ጉዳይ ማወዛገቡ ቀጥሏል።ምንም እንኳን 6 የአውሮጳ ሃገራት ስደተኞቹን ለመቀበል ፈቃደኝነታቸውን ቢያሳውቁም ከመርከቡ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው ኢጣልያ ግን ዛሬም እንደጨከነችባቸው ነው።ስፓኝ ለመርከቧ ማረፊያ ሁለት አማራጭ ወደቦችን ብትፈቅድም ባለቤቶቿ በርቀታቸው ምክንያት አልተስማሙም።በዚህ መሀል መርከቧ የጫነቻቸው ስደተኞች እየተንገላቱ ነው።